16ኛው የኢትዮጵያ የወባ ምርምር ኔትወርክ ሲምፖዚየም እና የብሔራዊ የወባ መርሃ ግብር የዘጠኝ ወራት የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነዉ _____________ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፣ ሲምፖዚየሙ ሳይንቲስቶችን፣ ፖሊሲ አዉጪዎችን እና ወጣት ፈጠራ ባለሞያዎችን በአንድ ማዕቀፍ ያሰባሰበና እና የእውቀት ልውውጥን የሚያበረታታ መድረክ ነው ብለው ወባ በኢትዮጵያ ለህዝብ ጤና፣ ለኢኮኖሚ ልማት እና ለማህበራዊ ደህንነት ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑንም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ በመልዕክታቸው የዘንድሮው ሲምፖዚየም ጭብጥ “የወባ ቁጥጥርን ማቆየት እና ማጥፋትን ማጠናከር በአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብና አዳዲስ ሳይንሳዊ ፈጠራዎችን በመጠቀም” መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ አቅጣጫ የተቀናጀ እና ቀጣይ ስራ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የወባ ምርምር ስራዎች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው፣ የጤና ምርምርን በአገር ውስጥ ፋይናንስ ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን አስነስተዋል። በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ህይወት ሰለሞን በበኩላቸዉ ወባ መከላከል የሚቻል ቢሆንም አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ የጤና ችግር ስለሆነ ሁሉም በለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ከሀገር ውስጥና ከውጭ የመጡ ተመራማሪዎች ፣ የጤና ባለሙያዎች እና አጋር ድርጅቶች የተሳተፉት መድረኩ በጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የተዘጋጀ ሲሆን ሲሆን፣ የብሔራዊ የወባ መርሃ ግብር የዘጠኝ ወራት አፈጻፀም ሪፖርትም ቀርበዉ ዉይይት ተካሂዷል።